የውጭ ግንኙነት ፕሮግራም

የውጭ ግንኙነት ዋና ዓላማ፡- ሀገራዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት

ፓርቲያችን የውጭ ጉዳይን ከሀገር ውስጥ ጉዳይ የተነጠለ አድርጎ አይመለከትም። ይልቁንም የሀገር ውስጥ ጉዳያችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ለውጦች ነፀብራቅ ሆኖ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ያልዘነጋ ነው። የውጭ ግንኙነታችንም የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታን የሚያረጋግጥ፤ የሀገር አንድነትን በማስጠበቅ ሀገራዊ ክብርን የሚያጎናጽፍ፤ ሀገራዊ ክብርን በማጎናጸፍ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ይሆናል። ሀገራዊ ክብር የሌለው ሀገር ሀገራዊ ጥቅሙን ሊያስጠብቅ እንደማይችል ፓርቲያችን በጥብቅ ይገነዘባል። በመሆኑም የኢትዮጵያን ታሪክ እና አንድነት እንዲሁም የዜጎቿን ክብርና ተስፋዋን የሚያንፀባርቅ የጋራ ስምምነት ያለው ሀገራዊ ክብርን እና ሀገራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅ የተቀናጀና የተማከለ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ትግበራን እውን ያደርጋል። ሀገራዊ ክብራችንን ለማረጋገጥ እና ጥቅሞቻችንን ለማስከበር፣ አስቀድሞ ግንኙነትን በማደስና በማጠናከር ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን መሥራት ላይ ትኩረት በማድረግ በግንኙነት ብልሽት ምክንያት የምናጣቸውን ሀገራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር አመች ሁኔታ ይፈጥራል። በውጭ ግንኙነት መስክ ሀገራችን መልካም የሚባል ውጤት ያስመዘገበች ሀገር ብትሆንም የውጭ ግንኙነታችን ከጉድለት እና ከግድፈት የጸዳ አይደለም። ስለዚህ ግድፍቶቹን እና ጉድለቶችን መለየት፣ ማስተካከል እና መሙላት እንዲሁም የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ማስቀጠል የፓርቲያችን የውጭ ግንኙነት መሠረቶች ናቸው።

የውጭ ግንኙነት ግቦች

  1. ሀገራዊ ክብርን የሚያረጋግጥ የውጭ ግንኙነት
  2. ለትብብርና ለጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት በመስጠት አጋሮቻችንን ማስፋት
  3. የብዙዮሽ ትብብር ተቋማት ተሰሚነትን መጨመር እና ፖሊሲያዊ ነጻነትን ማስከበር
  4. ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ
  5. የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ማሳደግ
  6. ሀገራዊ ክብርን እና ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የውጭ ግንኙነት የመፈፀም አቅም መገንባት